ዳያስፖራው በዘንድሮው በጀት ዓመት አምስት ወራት ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት መላኩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
በበጀት ዓመቱም አራት ቢሊየን ዶላር ከሬሚታንስ ለመሰብሰብ መታቀዱን አመልክቷል።
ዳያስፖራው በ’አይዞን ኢትዮጵያ’ የገንዘብ ማሰባሰቢያ አማራጭ እና በውጭ አገራት በሚገኙ ሚሲዮኖች አማካኝነት ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ400 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።
በ’አይዞን ኢትዮጵያ’ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ256 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ ለተፈናቀሉ ወገኖች መሰብሰቡም ተጠቁሟል።
ዳያስፖራው በአምስቱ ወር ለአገር መከላከያ ሰራዊት ከ103 ሚሊየን ብር በላይ በገንዘብና በአይነትና ለገጽታ ግንባታ ስራዎች ደግሞ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ነው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ያስታወቀው።
በአምስት ወራቱ በኢንቨስትመንትና ንግድ ላይ ለመሰማራት የ22 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 339 ዳያስፖራዎች ፍላጎት ማሳየታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
ዳያስፖራው ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት 9 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት መላኩም ተመላክቷል።
(ኤፍ ቢ ሲ)