“አንድ ሆነን ድምፃችንን እናሰማለን፤ አንድ ሆነን ጠንካራ ክንዳችንን እንሰነዝራለን!” በሚል መሪ ቃል ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ሴቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ዘርፈሸዋል ንጉሴ በውይይቱ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ጁንታው ኢትዮጵያን ያለ ልክ በመካድ እና ሀገር የመከፋፈል ዓላማ አንግቦ እያደረገ ባለው ጦርነት እኛ ሴቶች የትኛውንም መስዋዕትነት ቢያስከፍልም ወደኋላ የማንል መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል ።
አድዋን የደገመች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማስረከብ ከምን ጊዜውም በላይ አከባቢያችንን በመጠበቅ ረገድ የድርሻችንን መወጣት አለብን ያሉት ወ/ሮ ዘርፈሸዋል ጁንታውን እየተከተለ ድል እየነሳ ያለውን የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ልዩ ልዩ የጸጥታ አካላትን የመደገፍ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አሳስበዋል ።
ጁንታውና የትግራይ ተወላጅ አንድ እንዳልሆኑ የገለጹት የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ም/ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ አሁን ያለው ጦርነት የኢትዮጵያን አንድነትና ልማት በማይፈልጉ የውጭ ሀይሎች በእጅ አዙር የሚደረግ ጦርነት መሆኑን በመገንዘብ ሁላችንም በመተባበር፣ በመተጋገዝ እና በእህትማማችነት መንፈስ በያለንበት የድርሻችንን ሚና መወጣት ከቻልን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ወቅት ማለፍ እንችላለን በማለት ገልጸዋል ።
እኛ እያለን ልጆቻችን ሀገር አያጡም ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያን ለመበታተን ቆርጦ የተነሳውን አሸባሪ የህወሓት ቡድንን ስንቅ ከማዘጋጀት ጀምሮ እስከ ግንባር ድረስ በመሰለፍ ኢትዮጵያ ለማዳን ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ ነን ሲሉ ገልጸዋል
ጁንታው መበስበስ እንጂ ማበብ አንፈልግም ያሉት የከተማዋ ሴቶች አከባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ እና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን መቆማቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል ።
በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የከተማዋ ሴቶች የውይይት መድረክ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ዘርፈሸዋል ንጉሴ በተጨማሪ የሴት አደረጃጀት ኃላፊዎችና የከተማዋ ሴቶች የተገኙ ሲሆን የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት የውይይቱ መድረኩ ተጠናቋል ።