“ ግብር ለሀገር ክብር ” በሚል መሪ ቃል በ2014 ዓ/ም ግብራቸውን በታማኝነት ለከፈሉ ከ300 በላይ ለሚሆኑ ግብር ከፋዮች የምስጋና እና የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሚገባቸውን በመውሰድ የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ግዴታቸውን ለተወጡ ግብር ከፋዮች እውቅና ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ልዩ መስተንግዶ እና የቅድሚያ አገልግሎት እንዲያገኙ እናደርጋለን ብለዋል::
የገቢ አሰባሰብ ስርዓታችንን በማዘመን ገቢያቸውን የሚሰውሩ ፣ ያለደረሰኝ ግብይት የሚፈፅሙ እና የሚያጭበረብሩ ግብር ከፋዮች በመለየት ወደ ህግ እናቀርባለን ያሉት ከንቲባ አዳነች በቀሪው ግዜ ግብር ከፋዩች የመንግስትን ለመንግስት በመስጠት ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል::
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የልማት ስራዎች ከግብር ከፋዩ ህብረተሰብ በሚሰበሰብ ገንዘብ እንደሚሰሩ ጠቅሰው ከተማውን የሚመጥን የመሰረተ ልማት አቅርቦት ለማዳረስና የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን ፣ ግብር የሚሰውሩ አካላትን በመከታተል እና እርምጃ በመውሰድ እንዲሁም ፈፃሚውን በማብቃት የተሻለ ግብር እንዲሰበሰብ በማድረግ ነው ብለዋል::
በመድረኩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ የፌደራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣ ግብር ከፋዮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል::