በአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አዘጋጅነት “የዉይይት ዕሴት ባህልን ለማዳበር የሃይማኖት ተቋማት አስተዋፅኦ” በሚል ርዕስ የሃይማኖት አባቶች ዉይይት አደረጉ።
በቦሌ ክ/ከተማ አስተዳደር በተከናወነው የዉይይት መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ የሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ቀነዓ ያደታን ጨምሮ በርካታ የሃይማኖት አባቶች እና የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈውበታል።
በዉይይቱ መክፈቻ ስነስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ የየዕለት ማሕበራዊ ክንውናችን አካል በማድረግ ችግሮችን በየደረጃው የሚፈቱበት ባሕልን ሊያዳብር ያለውን የውይይት ዕሴት ሊያስጠብቅ የሚችል እንደሆነ የጠቀሱ ሲሆን የሃይማኖት ተቋማት አስተዋጽኦም ወሳኝ እንደሆነ አንስተዋል።
እንደ መጋቢ ታምራት ገለፃ ከሆነ ቀድሞ የተፈጠሩትንም ይሁን አዳዲስ ችግሮችን ለመፍታት እና የተረጋጋ ሕይወት እየመራን ከድህነት ለመውጣት ለምናደርገው ትግል ውይይት መልካም እድሎችን ይፈጥራል ብለዋል።
ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት በአሁኑ ሰዓት ለሃገራችን ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ ነው ያሉት ደግሞ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን ያቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ የሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ክቡር ዶ/ር ቀነዓ ያደታ ናቸው።
የእምነት ተቋማት ዜጎች መልካም ስነምግባር እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ስራ እየሰሩ እንደሆነ የጠቀሱት ዶ/ር ቀነዓ ያደታ አሁንም ቢሆን ግጭቶችን በውይይት ከመፍታት አንጻር የእምነት ተቋማት ሚና ትልቅ ነው አያይዘውም ይህ ዛሬ የተጀመረው የውይይት መድረክ ለአካታች ሀገር አቀፍ ውይይት ጥሩ ግብዐት ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።
በውይይት መድረኩ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ለውይይት መነሻ የሚሆን ሰፋ ያለ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በጽሁፋቸው ውስጥም የውይይት ዕሴት በሃይማኖት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለሁ አብራርተዋል።
ተሳታፊዎች በቀረበው የመነሻ ጽሁፍ ዙሪያ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ውይይቱን የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ጸጥታ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ክብረት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እና የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅራቢ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ከተወያዮች ለተነሳው ጥያቄ እና አስተያየት ምላሽ ሰጥተዋል።
በውይይት መድረኩ በመገኝት የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራው አባቶች ችግሮችን ለመፍታት እስካሁን ሲታደርጉ የነበረውን ጥረት አሁንም አጠናክራችሁ ቀጥሉ እኛም አብረናችሁ ለመስራት ቃል እንገባለን ብለዋል።
በዛሬው እለት የተጀመረው የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ለተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች በ11ዱም ክ/ከተማ የሚያደርገው የውይይትና የምክክር መረሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ እስከ የካቲት ወር ማብቂያ ድረስ የሚቀጥል ሲሆን በነገው እለት በአዲስ ክ/ከተማ የሚቀጥል ይሆናል።