ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ዛሬ በተለያዩ አካባቢዎች የተካሄደው ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡
በወርሃ ሰኔ በተከናወነው ምርጫ ወቅት በልዩ ልዩ ምክንያቶች ምርጫውን በወቅቱ ማከናወን ባልተቻለባቸው አካባቢዎች ምርጫ ቦርድ በያዘው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት ዛሬ አከናውነዋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚኖሩ የኮንታ፣ የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የከፋ፣ የዳውሮና የሸካ ሕዝቦች መተዳደር የሚፈልጉበትን የአስተዳደር ክልል በሕዝበ ውሳኔአቸው አሳውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “ሁለቱም የዴሞክራሲ ሂደቶች ላይ በነጻነት ፍላጎታቸውን በድምጻቸው መፈጸም ለቻሉ ዜጎቻችንን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ” ብለዋል ።
“እነዚህ ሰላማዊ የሆኑ የዴሞክራሲ ልምምዶች በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ምርጫ በማስፈጸም ሂደት ውስጥ የተካፈላችሁ አካላት በሙሉ፣ በወንድማማችነት እሴት ላይ ኢትዮጵያዊ መልክ ይዞ እየተገነባ ለሚገኘው ሕብረ ብሔራዊ የዴሞክራሲ ሥርዓታችን መዳበር አሻራችሁን አኑራችኋልና ኢትዮጵያ ታማሰግናችኋለችም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።