የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በዘመናት ውስጥ የፀና የሀገር ምሶሶ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሉዓላዊት ሀገር፣ ህዝቧ እንደነፃ ዜጋ ፀንተው የመኖራቸው ዐቢይ ምክንያት ለሀገራቸው ክብር፣ ለሰንደቅ ዓላማቸው ከፍታና ለዜጎች ነፃነት የሚዋደቁ ጀግኖች ወታደሮች በመኖራቸው ነው።
እንኳን በዚህ በዘመናዊው ዓለም፣ በጥንቱም ጊዜ የሀገርን ክብር ሊነኩ የሚመኙ ባዕዳን ሊወሩን ሲሞክሩ፣ ጀግኖች ጦር ጨብጠው፣ ደረታቸውን ለጥይት ሠጥተው እሳት ከሚተፉ ዘመናዊ መሳሪያዎች ጋር ለመተናነቃቸው ታሪክ ምስክር ነው።
ኢትዮጵያ በታሪኳ የሚዋደቁላት፣ ከጠላት የሚተናነቁ ጀግኖች አጥታ ባታውቅም፣ በዘመናዊ መልኩ የራሷን ሠራዊት በአዋጅ በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደረጃ ያቋቋመችበትንና የጦር ሚኒስቴር የሾመችበትን ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ/ም መነሻ በማድረግ በየዓመቱ ጥቅምት 15 ቀን የሠራዊት ቀን ሆኖ እንዲከበር ተወስኗል። ከዚህ ዓመት ጀምሮ ጥቅምት 15 ቀን የሠራዊታችን ቀን ሆኖ ይከበራል።
በዚህ ለኢትዮጵያ ህልውና ምሶሶ የሆነው የሠራዊታችን ቀን፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊትን የፀና ኢትዮጵያዊነትና ፣ ለሀገርና ለወገን የከፈለውንና እየከፈለ ያለውን ህያው መስዋዕትነት ይዘከራል።
የሀገር ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲወለበለብ፣ የወደቁ ጀግኖችን ታሪክ በክብር እናነሳለን። የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችንን በአስደናቂ ፍጥነትና ብቃት አደብ ማስገዛቱን በታላቅ አድናቆት እንዘክራለን።
ሠራዊታችንን መደገፍ ኢትዮጵያን መደገፍ ነውና፣ በማንኛውም ጊዜ ቦታና ሁኔታ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ኢትዮጵያችንን በክብር እናስቀጥላለን።
ክብር ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን!
እንኳን አደረሳችሁ!