በጎ ፍቃደኝነት ከበጎ ህሊና የሚመነጭ የተቀደሰ ተግባር ነው፡፡ ከራስ አልፎ ለሌሎች የመሆንን ፤አሳቢነትን አካፋይነትን አቋዳሽነትን፤ ተባባሪነትን ፤እኔ ብቻ አለማለትን ፤ተጋግዞና ተደጋግፎ መኖርን የሚገልፅ ከፍ ያለ ስብዕና መገለጫ ነው፡፡
በጎ ፈቃደኝነት የህብረተሰብን አኗኗርን ሊያሻሽሉና ሊለውጡ እንዲሁም ሃገርን ሊያሳድጉ የሚችሉ ተግባራትን፤ በራስ ተነሳሽነት፤ ተጨማሪ ክፍያ ወይም ምንዳ ሳይጠየቅበት የሚከወን ተግባር ነው፡፡ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ይህ የእርስ በርስ መደጋገፍ ለዘመናት አብሮን የኖረ ባህላችንም ጭምር ነው፡፡
መንግስትም ይህንን በጎ ተግባር ዕውቀቱ፣ ልምዱና ፍላጎቱ ያላቸውን ሰዎች ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እንዲገናኝ በማድረግ ተግባሩን በማስተባበር ወሳኙን ሚና ይጫወታል።
በዚሁ መሠረትም እንደ ሃገር ብሎም እንደ ከተማችን የበጎ ፍቃድ ስራዎችን ጀምረን በርካታ ሰው ተኮር ተግባራትን በማከናወን ውጤት የተመዘገበበት ስለመሆኑ ከተማችን በብዙ ሚሊዮን ሰዎች በበጎ ፍቃድ ስራዎች ተሳታፊነታቸውን በተጨባጭ አሳይነተውናል፤ ለጋስ እጆቻቸውን ዘርግተው በርካቶችን ደርሰዋል፡፡
ለበርካቶችም ድጋፍ እና አቅም አስታዋሽ መሆን ችለዋል፡፡ውስጥ በቅርቡ እንኳ የተመረቁት በአጭር ጊዜ እንደ አዲስ ተገንብተው የተጠናቀቁ የመኖርያ ቤቶች፤ የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት፤በበጎ ፍቃደኞች የተገነቡ የዳቦ ማምረቻና ማከፋፈያ ፋብሪካዎች ማስረጃዎች ናቸው። ስለሆነም በቀጣይ 2015 ዓ.ም ከነበረን ልምድ ወስደን የበጎ ፈቃድ አገልግሎታችንን በማሳደግ እና ባህል በማድረግ የከተማችን ገጽታ ከፍ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
ሁላችንም በበጎ ፈቃድ ካለን እውቀትና ሃብት ለማህበረሰባዊ ለለውጥ በማዋል የየራሳችንን አሻራ በማሳረፍ የከተማችን ብሎም የሃገራችንን እድገት ማፋጠን እንችላልን፡፡ ለተደጋገፉና ለተባበሩ እጆች ለውጥ ቀላል ነው፡፡በጎ ፈቃደኝነት ለራስ እርካታ ለሀገር እድገት ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡
የሀገሬን ህልውና ለማስከበር በበጎ ፈቃደኝነት ሁለንተናዊ ድጋፍ አደርጋለሁ!
መልካም የበጎ ፍቃድ ይሁንልን!!
በጎነት መልሶ ይከፍላል!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን አብዝቶ ይባርክ!!