የአምራችነት ቀንን ምክንያት በማድረግ ምክትል ከንቲባና የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አላፊ አቶ ዣንጥራር አባይ ፣የአዲስ አበባ ከተማ ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሹጉጤን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በአገር ወስጥ አምራቾች የተዘጋጁ አገር በቀል ምርቶችን ተዘዋውረው በመመልከት አምራቾችን አበረታተዋል ።
ኩራት በሀገር ምርት በሚል የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽንና ባዛርን ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅት ምክትል ከንቲባና የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዣንጥራር አባይ እንደተናገሩት ኢንተራይዞችን ወደ ኢንዱስትሪ በማሳደግ በአጠቃላይ ኢኮኖሚያችን መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ሁላችንም በተሰማራንበት ሁሉ በብቃት ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ብለዋል ።
በአብዛኛው ኢትዮጵያ በአምራችነት የዕድሜ ክልል ላይ ባሉ ወጣቶች የተገነባች ሀገር በመሆኗ በቅንጅት ተናበን ከሰራንና የየድርሻችንን ኃላፊነት በብቃት ከተወጣን ብልጽግናችንን በሚፈለገው ፍጥነት ማረጋገጥ እንችላለን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል
ኢንተርፕራይዞችንና ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ አገር በቃል ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የኢንዱስትሪውን ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ ፊት ማራመድ የሁላችንም የዘውትር ቀዳሚ ስራ መሆን ይኖርበታል ብለዋል ምክትል ከንቲባው
በናንተ በኢንተርፕራይዞችና የኢንዱስትሪ አንቀሳቃሾች ላይ የተመለከትነው የዓላማ ጽናት በሀገር አቀፍ ደረጃ ዜጎች ለአገር በቀል ምርቶች ያላቸውን አመለካከት በሚፈለገው ደረጃ የቀየረ በመሆኑ በዚህ ደረጃ መንቀሳቀስ ይጠበቅባችኋል ሲሉ ገልጸዋል ።
በአገራችን ከሚገኙ ኢንዱስሪዎች አርባ ከመቶው በከተማችን የሚገኝ ቢሆንም ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ አንጻር ቀሪ በርካታ ሥራዎችን በቅንጅት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል ምክትል ከንቲባው
ከተማ አስተዳደሩ ኢንደስትሪዎችን በክላስተር በማደራጀት ውጤት እንዲያስመዘግቡ ዘርፈ ብዙ እንቅሰቃሴዎችን የጀመረ ሲሆን አጠቃላይ በኢንዱስትሪዎችና በኢንተርፕራይዞች ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎች በመፍታት ምርትና ምርታማነት በቅንጅት በማሳደግ የአገራችንን ዕድገት መደገፍ ወቅቱ የሚጠይቀው ነው ብለዋል