13ኛው የአዲስ አበባ ከተማ የባህል ፌስቲቫል”የባህል እሴቶቻችን ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ ቃል በግዮን ሆቴል በትናንትናው እለት ተከፍቷል።
የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው ፥የፌስቲቫሉ ዋነኛ ዓላማ የማህበረሰቡን ወግ፣ ባህልና በጎ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶችን ማስተዋወቅ ነው ብለዋል።
13ኛ አመቱን ያስቆጠረውን የባህል ፌስቲቫል በቀጣይ በስፋት በማጠናከር በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል።
የብሔር ብሔረሰቦች የባህል፣ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ ባህላዊ የግጭት አፈታትና ሌሎች ክዋኔዎች ለህዝብ የሚተዋወቁ መሆኑን ጠቅሰው፥ ፌስቲቫሉ አምራቾችና ሻጮች የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩም የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ባህላዊ ምግብና መጠጦች፣ አልባሳት የዲዛይን ውድድሮችና ሌሎች ሁነቶች ይከናወንበታል ነው ያሉት።
በፌስቲቫሉ ላይ በክብር እንግዳነት የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚነስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ባህል፣ የአኗኗር ዘዬ ማሳያ መሆኗን ጠቅሰው እንደነዚህ ያሉ የባህል ፌስቲቫሎች መበረታታት ይገባቸዋል ብለዋል።
አገር በቀል እውቀቶች እንዳይጠፉ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተደግፈው ለትውልድ ማስተዋወቅና ማስተላለፍ ስለሚቻልባቸው አማራጮች ላይ የምሁራን ውይይት የሚካሄድ ይሆናል ተብሏል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ፌስቲቫል፥ የተለያዩ የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህል፣ አኗኗር እና አለባበስ የሚያሳዩ ትዕይንቶች ይቀርባሉ።