የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባካሄደው መደበኛ ስብስባው ለ2014 በጀት ዓመት 70 ቢሊየን 670 ሚሊየን ብር በጀት መወሰኑ ይታወቃል::
የበጀቱን አጠቃላይ ዝርዝር ሁኔታ በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤን ጨምሮ የከተማው ምክር ቤት የመንግስት በጀት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ኮሚቴ እንዲሁም የህዝብ አደረጃጀት ተወካዮች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ነጂባ አክመል በውይይቱ እንዳስታወቁት ረቂቅ በጀቱ በዋናነት የነዋሪውን ህይወት በተጨባጭ የሚያሻሽሉ እና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ለሚያስችሉ ዘርፎች ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል::
በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማጠናከር፤ ድህነትንና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚያስችሉ ወሳኝ ዘርፎችን ቅድሚያ በመስጠት መደልደሉን ወ/ሮ ነጂባ አክመል ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመንግስት በጀት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ኮሚቴ አመራሮች እና አባላት እንዲሁም የህዝብ አደረጃጀት ተወካዮች የተመደበው በጀት ከብክነት በጸዳ መልኩ በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል ክትትል እንዲደረግ አሳስበዋል::