አዲስ አበባችን እንደ ስሟ ውብ ፤ የምታኮራን እንድትሆን እናደርጋታለን፤ ይህንን ማንም ሊያስቆመን አይችልም!!-
ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ የሠላምና የአብሮነት ከተማ በሚል መሪ ቃል ከተማ አቀፍ አካል ብቃት እንቅስቃሴ(Mass Sport) በጉለሌ ክ/ከተማ ተካሂዷል፡፡
ጤናማና ብቁ አምራች ዜጋ ለመፍጠር ስፖርት ያለውን ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት እንዲሁም ስፖርትን በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ክ/ከተሞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በየሳምነቱ በቋሚነት እያዘጋጀ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በዛሬው እለት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በጉለሌ ክ/ከተማ በተካሄደው የማስ ስፖርት ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ወጣቶች ነዋሪዎችና የስፖርት ቤተሰቦች እንዲሁም ታዋቂ ሰዎችና አርቲስቶች አመራሮች ተሳትፈውበታል፡፡
በዚሁ ወቅት መልእክት ያስተላለፉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ይህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአዲስ አበባ ወጣቶች የሰላም የአንድነትና የአብሮነት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ ምንጊዜም ቢሆን ለስርዓት አልበኝነት ለመከፋፈል ምቹ አይደለችም፡፡ፈፅሞ ለዚህ አትሰራም፤ ለዚህም እጅ አትሰጥም! ያሉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች እናንተም ወጣቶች በሁሉ አካባቢ ይህንን እንቅስቃሴ ስታደርጉ ከተማችን ለስርዓት አልበኝነት አትመችም፤አብሮነቷ ይቀጥላል፤አንድነቷ ያብባል እያላችሁ ነው በማለት ለከተማዋ ወጣቶች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ አበባችን እንደ ስሟ ውብ ፤በአለም አቀፍ ደረጃ የምታኮራን እንድትሆን እናደርጋታለን፤ ያሉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ይህንን ማንም ሊያስቆመን አይችልም!! እኛ ልጆቿ አለን እንተጋለን እንሰራለን!! በማለት ተናግረዋል፡፡
የአካል ብቃት እንቅስቃሴው በመላው ከተማይቱ በሁሉም ክ/ከተሞች እና ወረዳዎች እየተካሄደ ይገኛል፡፡