ይህ ሁሉ ላንቺ ነው እናታለም!
Meserete Tadesse2022-05-26T08:42:23+00:00ማህጸነ ለምለሟ ኢትዮጵያ በያይነቱ ወልዳለች፤ ከጀግና እስከ ባንዳ፣ ለሀገሩ የገባውን ቃል ኪዳን ከሚያከብር እስከ ቃል አባይ፡፡ ይህች ሀገር፤ ጡቶቿን አጥብታ ሰው ባደረገቻቸው፣ አስተምራ ለወግ ማዕረግ ባበቃቻቸው የገዛ ልጆቿ በተደጋጋሚ ክህደት ተፈጽሞባታል፡፡ ለዘመናት ያጎረሱ እጆቿ ተነክሰዋል፡፡ ወተቷን ጠጥተው፣ ከሜዳዋ ቦርቀው፣ መአዛዋን ምገው ባደጉ ልጆቿ እናት ሀገር ከጀርባዋ ተወግታለች፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ባንዳ በሆኑ ልጆቿ ለውስጥም ለውጪም ጠላቶቿ ጥቃት ተጋልጣ ታውቃለች፡፡ የእናት ሀገር ጠላቶች በጦር አውድማ ሊያሳኩ ያልቻሉትን ዓላማ በአፍቅሮተ ንዋይና በስልጣን ጥማት የኖኸለሉ ድኩማን ልጆቿን ተጠቅመው ዓላማቸውን ለማሳካት ሲጥሩ አይታ ልቧ ደምቷል፡፡ ይህ በልጆቿ የመከዳት ሂደት ኢትዮጵያን በቅርቡ አጋጥሟታል፡፡ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል መንግሥት ባካሄደው የኅልውና ዘመቻ ወቅት ከላይ ለማተት የተሞከረው የታሪክ ዳራ ታይቷል፡፡ [...]